የቢሮ ኃላፊ መልዕክት
ትምህርት በሀገር ስልጣኔም ሆነ ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጠዉ ለዉጥና ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ በሌላ መንገድ ሲታይ በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት ደግሞ ለድህነታቸውና ለኋላ ቀርነታቸው ትልቁ ምክንያት ዜጎቻቸውን በበቂ ሁኔታ ማስተማር አለመቻላቸው ነው፡፡ወቅቱ እንደሀገር አዲሱን ሥርዓተ-ትምህርት በመተግበር ላይ ያለንበት እንደመሆኑ በኢፌዴሪ መንግስት ለትምህርት ትኩረት በመስጠት የገጠመንን የትምህርት ጥራትና ዉጤት ስብራት ለመጠገን በሚያስችል መልኩ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ያመላክታል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ትምህርት ቢሮ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ተደራጅቶ በክልሉ በሚገኙ 7 ዞኖቸና 3 ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ በሁሉም የመጀመሪያ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ለደረጃው የሰለጠኑ መምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮችን በመመደብ የትምህርት ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡
እንደ ሀገር ለረጅም ዓመታት ስንጠቀምበት የቆየነው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ተሸሽሎ በአዲስ ሥርዓተ-ትምህርት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤ/ቶች እየተተገበረ ያለ ሲሆን በ2016 ዓ/ም በተመሳሳይ ከ9-12ኛ ክፍሎች ላይ ሙሉ በሙሉ መተግበር ተጀምሯል፡፡በዚሁ መሠረት በክልላችን ሀገራዊ አቅጣጫን በመከተል የተማሪ ዉጤትና የጥራት ስብራቱን ለመጠገን እዲሆን በታሰበዉ አግባብ በዲሱ ሥርዓተ-ትምህርትና የፈተና ቢጋር አዘገጃጀት ላይ ለመምህራንና ለትምህርት ቤ/ት አመራሮች ሥልጠና በመስጠት መተግበር ተጀምሯል፡፡
በሁሉም የትምህርት ተቋማት የሚከናወነው ዋናው ቁልፍ ተግባር ለሀገር ልማትና ብልጽግና መሠረት የሆኑ ህፃናት በዕውቀት፣ ክህሎትና በጥሩ ስነምግባር ታንፀው እንዲያድጉ አስፈላጊውን ግብዓትና የሰለጠነ የሰው ሀይል ማቅረብ ነው፡፡ ስለሆነም ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በቅንጅት ቢሰሩ ለሀገር ዕድገት፣ ክብርና አንድነት የሚተጉ ምስጉን ዘጎችን ማፍራት እንችላለን፡፡
በመደበኛ ትምህርት ውስጥ ያላለፉ ወላጆች የተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ የማህበረሰቡን አስተሳሰብና የአኗኗር ዘይቤ ከመቀየሩም ባሻገር ወላጆች የትምህርት ጥቅም በአግባቡ ተረድተው ዕድሜቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤቶች እንዲልኩ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
ሀገር ተረካቢና በመልካም ሥነ-ምግባር የታነጹ ዘጎችን ለማፍራት ዋናዎቹ ተቋማት ትምህርት ቤቶች ናቸው። በትምህርት ቤቶች ደግሞ መምህራን የሚጫወቱት ሚና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍ ያለ ነው፡፡ መንግስት፣ ወላጆችና መንግሳታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተባብረው ግብዓትና የሰው ሀይል ቢያሟሉ እንኳን መምህራን በተገቢው ሁኔታ ተማሪዎቻቸው እንዲጠቀሙበት ካለደረጉና ተከታታይ የሆነ ድጋፍ ካላደረጉ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የቀረቡት ግብዓቶች ፋይዳቸው እምብዛም ይሆናል፡፡
ትምህርት ቤቶች የሚመሩት በትምህርት ቤት አመራር ነው፡፡ የአመራር ትልቁ ኃላፊነት በሚመራው ተቋም ውስጥ ባለው የሰው ኃይል ላይ መነሳሳትን በመፍጠር ስዎች በፈቃደኝነት ያላቸውን አቅምና ችሎታ አውጥተው እንድሰሩ ማድረግ ነው ፡፡ እናንተ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የክልሉ መንግስትና የትምህርት ቢሮ የጣለባችሁን ከፍተኛ ኃላፊነትና አደራ በመረዳት የተጀመረዉን የትምህርት ጥራት ዕዉን ለማድረግ የትምህርት ቤት ማህበረሰብና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በክልላችን የሚታየውን የትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሳደግ ትምህርት ቤቶችን በግብዓት፣ ሂደትና ውጤት መለኪያዎች ለመለካትና ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችል ዕቅድ በማቀድና በመተግበር ሀገራችን ከትምህርት ሴክተሩ የሚትፈልገውን ተልዕኮ ለማሳካት የመሪነት ሚናችሁን በከፍተኛ የሀላፊነት ስሜት እንዲትወጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
በጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም!!
አቶ አንተነህ ፈቃዱ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር፤ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ
Copyrights 2024. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE