በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሠለጠነና የተሻለ የሙያ ብቃት ያለው የትምህርት ቤት አመራር መፍጠር ያለመ የትምህርት ቤት አመራርነት ውድድር እየተካሄደ ነው።
በክልሉ ለሱፐርቫይዘርነት፣ ለሁለተኛ ደረጃ፣ ለአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ርዕሰ መምህርነትና ምክትል ርዕሰ መምህርነት ውድድር ተመዝግበው ዝቅተኛ የመወዳደሪያ መስፈርት ላሟሉ 4 ሺህ 970 ተወዳዳሪዎች በ10 ማዕከላት ክልላዊ የጹሑፍ ፈተና እየተሰጠ ነው።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ማልደዮና የምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ለምጃቦ በቡታጅራ የፈተና ማዕከል ተገኝተው ፈተናውን አስጀምረዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ማልደዮ እንዳሉት በክልሉ የትምህርት ሥርዓቱን በሠለጠነና የተሻለ የሙያ ብቃት ባለው የሰው ሀይል ለመምራትና የተጠያቂነት ስርዓት ለማስፈን የትምህርት ቤት አመራር ሪፎርም ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል።
ሪፎርሙን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያስችል የትምህርት ቤት አመራር ምልመላ፣ መረጣና ምደባ መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
በዚህም ለትምህርት ቤት አመራርነት የውድድር ማስታወቂያ በየአካባቢው ወጥቶ ተመዝግበው ዝቅተኛ የመወዳደሪያ መስፈርትን ያሟሉ 4 ሺህ 970 ተወዳዳሪዎች መለየታቸውን ጠቁመዋል።
ቢሮው ለተወዳዳሪዎች ክልላዊ የጽሑፍ ፈተና በከፍተኛ ጥንቃቄና በዩኒቨርሲቲ መምህራን አዘጋጅቶ በዛሬ ዕለት በተመረጡ 10 የፈተና ማዕከላት የጽሑፍ ፈተና እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የፈተና ማዕከላቱም ወራቤ፣ ሆሳዕና፣ ወልቂጤ፣ ዱራሜ፣ ቡታጅራ፣ ሀላባ ቁሊቶ፣ ሾኔ፣ ሀደሮ፣ ቆሼ እና ሳጃ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ለምጃቦ በበኩላቸው በክልሉ ለትምህርት ቤት አመራርነት ተወዳዳሪዎች የጽሑፍ ፈተናው በሦስት ዓይነት መልኩ ተለይቶ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ለሱፐርቫይዘር፣ ለሁለተኛ ደረጃ፣ ለአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ርዕሳነ መምህራንና ምክትል ርዕሳነ መምህራን መሆኑን ጠቁመዋል።
ፈተናው በ10 ማዕከላቱም ተጀምሮ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በይዲድያ ተስፋሁን
Copyrights 2024. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE