በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ2017 የትምህርት ዘመን መማር ማስተማር በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል እና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ማልደዮ በክልሉ ለ2017 የትምህርት ዘመን መማር ማስተማር ከነሐሴ 16 ጀምሮ የተማሪዎች ምዝገባ ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል።
በዚህም በመደበኛ 1 ሚሊዮን 204 ሺህ 128 ተማሪዎች እንዲሁም በቅድመ መደበኛ 304 ሺህ 94 ተማሪዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ከተማሪዎች ምዝገባ ጎን ለጎን ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱንም ኃላፊው ገልጸዋል።
በተለይም ትምህርት ቤቶችን የማስዋብ፣ የተመዘገቡ ተማሪዎችን በክፍል መደልደል፣ የመምህራንና የክፍለ ጊዜ ድልድል ማውጣትን ጨምሮ መምህራን የትምህርት ዕቅድ አውጥተው ለመማር ማስተማር ዝግጁ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ መሰራቱን አመላክተዋል።
ዛሬ መስከረም 7/2017 ዓ.ም የ2017 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ክፍለጊዜ የተጀመረ ሲሆን በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ተገኝተው እየተማሩ እና መምህራንም እያስተማሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሳማኝ ምክንያት ያልተመዘገቡ ተማሪዎች እንዲመዘገቡና በማካካሻ ትምህርት ታግዘው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋልም ብለዋል።
የትምህርት ዘመኑን የመማር ማስተማር ሥራ በተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት መጀመር የዓመቱን የትምህርት ይዘት በጊዜ ለመጨረስና ተማሪዎችም በተገቢው እንዲረዱት ከማድረግ አንጻር ፋይዳዉ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ወላጆች ልጆቻቸውን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በይዲድያ ተስፋሁን
Copyrights 2024. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE