ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ አዲሱን ዓመት አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሙሉ መልዕክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል።
መላው ኢትዮጵያውያን እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝቦች እንዲሁም በየትምህርት እርከኑ የምትገኙ ተማሪዎች፣ መምህራንና የትምህርት አመራሮች በሙሉ እንኳን ለ2017 አዲስ ዓመት አደረሳችሁ አደረሰን፡፡
በሀገራችን ትምህርት ስርዓት ላይ ያጋጠመውን ስብራት እና የትምህርት ጥራት ጉድለት በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ለትምህርት ልማት ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ በመንደፍ ተግባራዊ አድርጓል።
ይህም ለሀገር በቀል እውቀቶች ልዩ ትኩረት የሰጠና ዜጎች ሁለንተናዊ እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ይዘው እንዲቀረጹ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ነው።
በክልላችንም የትምህርት ጥራትና ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ በርካታ ተግባራቶች ተከናዉነዋል። በተጠናቀቀው የ2016 ዓመት በክልሉ ትምህርት ዘርፍ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል።
ለአብነት በዓመቱ በትምህርት ቤቶች ምቹ ሁኔታና አካባቢ ለመፍጠር በ"ትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄ 1 ነጥብ 1 ቢልዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል። በዚህም 109 ትምህርት ቤቶች፣ ከ1 ሺህ 4 በላይ የመማሪያ ክፍሎች፣ 134 ቤተ ሙከራና ቤተ መጽሐፍቶች አዲስ ግንባታ፤ 74 ሺህ በላይ የተማሪ መቀመጫዎች ግዢ፤ 991 ትምህርት ቤቶች ከ 5ሺህ 1 መቶ በላይ የመማሪያ ክፍሎች ጥገና ስራ ተጠቃሽ ነው።
በክልሉ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ ለማስቀረት ከመጋቢት 20/2016 ዓ.ም ጀምሮ በ2 ልዩ ወረዳዎች እና በ11 ወረዳዎች የምገባ ፕሮግራም እንዲጀመር ተደርጓል። በዚህም በ66 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 54 ሺህ 671 ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
በዓመቱ በሀገራዊና በክልላዊ ፈተናዎች የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል መንስኤዎች ዙሪያ ክልላዊ ጥናት ተደርጓል። በጥናቱ አንዱ መንስኤ ተደርጎ በተመላከተው የትምህርት ቤት አመራሮች ማለትም ርዕሰ መምህራን፣ ምክትል ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች ስራቸውን በብቃት መወጣት እንዲችሉ፣ ውጤታማ እንዲሆኑ እና ሃላፊነታችውን በተጠያቂነት በመወጣት የትምህርት ጥራት እና የተማሪዎች ክልል-አቀፍና አገር-አቀፍ ፈተናዎች ውጤት ለማሻሻል የትምህርት ቤት አመራር ሪፎርም መመሪያ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
ሪፎርሙ የሰለጠነ ጠንካራ የትምህርት ቤት አመራር ሽፋን ለማሳደግ፣ ብቁ ሆነው ለትምህርት አመራርነት ዕድል ላላገኙ ዕድል ለመፍጠር፣ ሴት የትምህርት አመራሮችን ተሳትፎ ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
በሌላ መልኩ ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል መንስኤ ተብለው በተለዩ ጉዳዮች ላይ ቢሮው በክልሉ ከሚገኙ 3ቱ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ ጋር በጥምረት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል።
የማጠናከሪያ ትምህርትን ጨምሮ ለ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሞዴል ፈተና አዘጋጅቶ መስጠት እና የፈተና አስተዳደር መመሪያ የማሻሻልና ስራ ላይ ማዋል የመሳሰሉ ተግባራት ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የትምህርት ጥራትና ተገቢነትን ከማረጋገጥ አንጻር የስርዓተ ትምህርት ትውውቅና ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች በሁለት ዙር ስለጠና ተሰጥቷል።
በክልሉ አዲሱ ስርዓተ ትምህርትን በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ሙሉ ትግበራ እንዲውል ከትምህርት ሚኒስቴር የመጣውን ከ1 ሚልዮን 116 ሺህ በላይ መጽሐፍት በሁለት ዙር ስርጭት ተደርጓል። በሌላ መልኩ በክልሉ ከቅድመ አንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የመማሪያና የማስተማሪያ መጽሐፍ በራስ አቅም ለማሳተም ከ326 ሚሊዮን 247 ሺህ ብር በላይ በህብረተሰብ ተሳትፎ በማሰባሰብ 1 ነጥብ 3 ሚልዮን በላይ መጽሐፍ ታትሞ ለትምህርት ቤቶች ተሰራጭቷል።
ከመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት አንጻር የዕጩ መምህራን መመልመያ መስፈርት መቀየርና 4 መቶ 50 ብር የነበረውን የኪስ ገንዘብ ወደ አንድ ሺህ ብር ማሳደግ ተችሏል። በማስተማር ስነ- ዘዴ ላይ ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መምህራን በሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ አማካኝነት በየሳምንቱ መጨረሻ ለአራት ወራት የቆየ የስራ ላይ ስልጠና ተሰጥቷል።
በዚህም በዓመቱ ተጨባጭ ለውጥ የመጣ ሲሆን በክልሉ በ2016 ዓ.ም 1መቶ 10ሺህ 772 መደበኛ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከወሰዱት ውስጥ 48 ሺህ 728 ወይም 44 በመቶ ያህሉ 50 በመቶና በላይ አምጥተዋል። በዓመቱ የተመዘገበው ውጤት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ138% ዕድገት ያሳየ ነው ።
በአገር-አቀፍ ፈተና በ2015 ትምህርት ዘመን 2.7% የክልሉ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን በ2016 ትምህርት ዘመን ከተፈተኑት የክልሉ ተማሪዎች 3.4% ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አስመዝግበዋል።
በዓመቱ 8 ሺህ 6 መቶ 80 መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች በ37 የትምህርት ዓይነቶች ምዘና ወስደዋል። ከዚህም ውስጥ 2 ሺህ 586 ሴቶች ናቸው።
በክልሉ በተማሪዎችንና በመምህራን የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎችን ለማበረታታት ለመጀመሪያ ጊዜ ክልላዊ የሳይንስና ፈጠራ ስራ አውደ-ርዕይ እና ውድድር ተካሂዶ ለፈጠራ ስራ ባለቤቶች እውቅና ተሰጥቷል።
በክልሉ በአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ከተመዘኑ 993 የ1ኛ እና መካከለኛ፣ የሁለተኛ ደረጃና የምዕራፍ 3 ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 3 ናቸው። ከአጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ደግሞ ደረጃ 4 ያሟላ እንድም ትምህርት ቤት የለም ስለዚህ በቀጣይ በዘርፉ በልዩ ትኩረት መስራት ያስፈልጋል።
ቢሮው በአዲሱ ዓመትም በክልሉ ትምህርት ዘርፍ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ትጋቱን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት በማሟላት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ብርቱ ጥረት ይደረጋል።
የትምህርት ቤት አመራር ሪፎርም ተግባራዊነት ለትምህርት ጥራት ጉልህ ሚና ስላለው የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አሁን ወቅቱ የ2017 የትምህርት ዘመን ትምህርት የሚጀምርበት በመሆኑ ዕድሜያቸዉ ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ በማምጣት የትምህርት ተሳትፎን ለማረጋገጥ በትኩረት እንሰራለን።
ደረጃቸዉን የጠበቁ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤቶችን ተደራሽ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የተማሪዎችን ዉጤት ለማሻሻል እንሰራለን።
በሴክተሩ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቁርጠኝነት ለመፍታት የምንተጋ ይሆናል።
በክልሉ ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል በ2017 የትምህርት ዘመን በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሙያ ትምህርት መሰጠት ይጀምራል።
የትምህርት መረጃ አያያዝን በማዘመን ተዓማኒና ወጥነት ያለው የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ይሰራል።
በዓመቱ በመምህራን ልማት እና አቅም ግምባታ ስራዎች በልዩ ትኩረት ይፈጸማሉ። የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ብቃታቸውን በምዘና የማረጋገጥና የሙያ ፈቃድ መስጠት ስራ በትኩረት ይሰራል።
ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮች ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የመላው ህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
ባለፈው ዓመት በትምህርቱ ሴክተር ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች በማስቀጠል ክፍተቶቻችን ለማረምና ለላቀ ስኬት በአዲስ መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንሰራ ይገባል።
ባለሀብቶች፣ በውጭ ሀገራት ያሉ ዜጎች ህብረተሰቡና አጠቃላይ ባለድርሻ አካላት በ"ትምህርት ለትውልድ" እና በ"መጽሐፍት ህትመት ሀብት አሰባሰብ" ንቅናቄ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በራሴና በክልሉ ትምህርት ቢሮ ስም ምስጋና አቀርባለሁ።
በየደረጃው "ትምህርት ለትውልድ" እና "የመጽሐፍት ህትመት ሀብት አሰባሰብ" ንቅናቄ አጠናክሮ በማስቀጠል የትምህርት ቤቶችን መሠረተ-ልማት በማሟላት የትምህርትቤቶችን ደረጃና የተማሪዎችን ዉጤት ማሻሻል ያስፈልጋል።
በ2016 ትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻ ጥሩ መሠረት የተጣለ በመሆኑ በ2017 የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ ይሰራል።
በዚህ ረገድ የክልሉ ህዝብና ባለድርሻ አካላት በአዲሱ ዓመትም የተለመደውን ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቀርባለሁ።
አዲሱ ዓመት በሁሉም መስክ የላቀ ውጤት የሚመዘገብበት የህብረተሰብ ተጠቃሚነትን በጋራ ትብብር እውን የሚሆንበትና የመሻገር ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞቴን እየገለጽኩ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣የመረዳዳትና የደስታ እንዲሆንልን እመኛለው።
አቶ አንተነህ ፈቃዱ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ
ጳጉሜ 5/2016 ዓ.ም
Copyrights 2024. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE