የማህበራዊ ክላስተር ተቋማት በስልጤ ዞን በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበራዊ ክላስተር ተቋማት በስልጤ ዞን ስልጢ እና ምስራቅ ስልጢ ወረዳ በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አደጋው በተከሰተበት ስልጢ ወረዳ ጎፍለላ ቀበሌ ተገኝተው ተጎጂዎችን ጎብኝተዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድርሩ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ከዚህ ቀደም እንደ ክልል ተጎጂዎችን የመጎብኙትና የመደገፍ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።
ዛሬ መቀመጫችን ወራቤ ያደረግን የማህበራዊ ክላስተር የክልል ተቋማት ተጎጂዎች ብቻችሁን አለመሆናችሁን እና እኛም ከእናንተ ጋር መሆናችንን ለማሳየት ነው የመጣነው ብለው በቀጣይም በአስፈላጊው ሁሉ ከጎናቸው እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
የክላስተሩ ተቋማት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ፣ አልባስና የህክምና መገልገያ ቁሳቁስ ማበርከታቸውን የሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሀመድናስር ገልጸዋል።
የአደጋው ተጎጂዎች ተቋማቱ ከጎናቸው መሆናቸውን በማሳየታቸው እንዲሁም በዛሬው ጉብኝት እና ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በድጋፍ ርክብክቡ የጤና፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የፐብሊክ ሰርቪስና የሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኃላፊዎችና የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ ተገኝተዋል።
በይዲድያ ተስፋሁን
Copyrights 2024. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE